በአዋጅ ቁጥር 230/2008 በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተሻሻለዉ የአስፈጻሚ አካላት ማቋቋሚያ፣ ማደራጃና ስልጣንና ተግባራትን መወሰኛ አዋጅ መሰረት ለቢሮው የተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት የሚከተሉት ናቸዉ፡፡ በሌሎች ህጐች አስቀድሞ የተደነገገው ወይም ወደፊት የሚደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ የክልሉ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ በዚህ አዋጅ መሰረት የሚከተሉት ዝርዝር ስልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡፡
- የክልሉ የውሃ ሃብት መረጃዎች በመሰብሰብ፣ በማደራጀትና በመተንተን ለልማት ስራዎች ያውላል፣ እንዲውል የደርጋል፣
- የክልሉን የውኃ ሃብት ክምችትና ስርጭት ያጠናል፣ እንዲጠና ያደርጋል፣ ያስተዋውቃል፣
- የክልሉ የውሃ ሀብት ዘላቂና አስተማማኝ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የሚያስችሉ ስልቶችን ይቀይሳል፣ ተግባራዊነታቸውን ይከታተላል፣
- የክልሉ ውሃ ሃብት ለማልማትና በጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ የፈቃድ አገልግሎት ይሰጣል፣ ተግባራዊነቱም ይከታተላል፣
- የክልሉ የውሃ አካላትና ተቋማት ከብክለትና ከአደጋ ስለሚጠበቁበት ሁኔታ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር ተባብሮ ይሰራል፣
- በክልሉ መንግስት አማካኝነት የተገነቡ የመስኖ ግድቦችን፣ ቦዮችንና ሌሎች አውታሮችን ተረክቦ ያስተዳድራል፣ይንከባከባል፣ይጠግናል፣ስለአጠቃቀማቸውም ዝርዝር የአሰራር ስርዓቶችን ይዘረጋል፣
- በፊደራሉ መንግስት አማካኝነት በክልሉ ውስጥ ለሚካሄዱ የውሃ ልማት ኘሮጀክቶች ክንውን በባለቤትነት ድጋፍ ያደርጋል፣
- በከተማም ሆነ በገጠር አካባቢዎች ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፍንን ለማሳደግ የአዳዲስ ጥናትና ዲዛይን የማሻሻያና የማስፋፊያ ስራዎችን እንዲካሄዱና ግንባታቸው እንዲከናወን ያደርጋል፣ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ያካሂዳል፣
- በከተማና በገጠር አካባቢዎች ለንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት የተገነቡ ተቋማት ዘላቂና አስተማማኝ አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዲኖራቸው ሙያዊ ድጋፍ ይሰጣል፣
- በክልሉ ውስጥ ወጥነትና ፍትሃዊነት ያለው የውሃ ታሪፍ፣ ሮያልቲና የወጭ አመላለስና አወሳሰን ስርዓት ቀርጾ ለክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ያቀርባል፣ ሲፈቀድም በስራ ላይ እንዲውል ያደርጋል፣ ይህንኑ አስመልክቶ በየጊዜው ጥናቶችን ያካሂዳል፣ በሌሎች እንዲካሄድ ያደርጋል፣
- በክልሉ ውስጥ የሚገኙት የመስኖና የገጠር መጠጥ ውሃ ተጠቃሚዎች ማህበራት ያደራጃል፣ ይመዘግባል፣ ይከታተላል፣ ይደግፋል፣
- በክልሉን የውሃ ሃብት ለመስኖ አገልግሎት ለማዋል የጥናትና ዲዛይን ስራዎችን ያከናውናሉ፣ በሌሎች ያሰራል፣ግንባታቸው ጥራቱን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ በማድረግ ለተጠቃሚዎች ያስረክባል፣
- በመስኖ ልማት ስራዎች ለሚሳተፍ አጋር አካላት ሙያዊ ድጋፍ ይሰጣል፣ የሚገነቡ የመስኖ አውታሮች ስታንዳርዳቸው የጠበቁ እንዲሆኑ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል፣
- የተገነቡ የውኃ ተቋማት ዘላቂና ተፈላጊውን አገልግሎት እንዲሰጡ የከፍተኛና መለስተኛ ጥገና ስራዎችን ያካሂዳል፣ እንዲካሄድ ያደርጋል፣
- ከውኃ ስራዎች ጋር የተያያዙ ቴክኖሎጅዎች ጥራታቸውን የጠበቁና ስታንዳርዳቸውን ያሟሉ መሆናቸውን ያረጋግጣል፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመፈተሽ ወደ ስርጭት እንዲገቡ ፈቃድ ይሰጣል፣ ያበረታታል፣
- ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በውሃ ሃብት ላይ የሚደረጉ ጥናቶችንና ምርምሮችን ያካሂዳል፣ ያስተባብራል፣ የምርምር ውጤቶችንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በክልሉ ውስጥ ያስፋፋል፣
- የክልሉን የውሃ ሃብትና የውሃ አቅርቦት ተቋማት በአግባቡ ለመጠበቅና ለመጠቀም የህብረተሰቡን የባለቤትነት ስሜት የሚዳብሩና በዘርፍ የተሰማሩትን አካላት ክህሎት የሚያሳድጉ ስልጠናዎችን ያዘጋጃል፣ ይሰጣል፣
- በክልሉና በፊዴራሉ መንግስት አካላት የሚወጡ የውሃ ሃብት አስተዳደር ህጐች፣ ደንቦችና መመሪያዎች በክልሉ ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆኑ ያደርጋል፣
- ክልል አቀፍ የሆኑ የውሃ ሃብት አስተደደር ፓሊሲ፣ ህግና ደንብ ረቂቆችን፣ መመሪያዎችን፣ ስትራቴጃዊ እቅዶችን፣ ስታንዳርዶችን የስራ ማንዋሎችን ያዘጋጃል፣ ያሰራጫል፣ተግባራዊነታቸውን ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፣
- በክልሉ ውስጥ የኢነርጂ ልማት እንዲስፋፋ ጥናቶችን ያካሂዳል፣ በሌሎች እንዲጠኑ ያደርጋል፣
- የግል ባለሃብቶች በኢነርጂ ልማት ስራዎች በስፋት እንዲሳተፉ ያነሳሳል፣ የተለያዩ የኘሮሞሽን ስራዎችን በማከናወን ያበረታታል፣
- በክልሉ ውስጥ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማምረት በሚያስፈልገው ሜጋ ዋት መጠን ላይ አግባብ ካላቸው የፊዴራሉ መንግስት አካላት ጋር ይመካከራል፣ እንደአስፈላጊነቱም የስልጣን ውክልና ሲሰጠው ኤሌክትሪክ የማመንጨትና የማሰራጨት ስራ ፈቃዶችን ይሰጣል፣ ይቆጣጠራል፣
- በገጠር ኢነርጂ አቅርቦት ረገድ የተለያዩ የኢነርጂ አማራጭ ቴክኖሎጂዎች በሰርቶ ማሳያ ሙከራ ተደግፈው እንዲስፋፋ ያደርጋል፣ የኢነርጂ ተጠቃሚዎችና የቴክኖሎጂ አምራቾች ተደራጅተው የብድር አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ ያመቻቻል፣
- በክልሉ ውስጥ የማገዶ ተክል በስፋት እንዲለማና አቅርቦቱ የህብረተሰቡን ፍጆታ የበለጠ እንዲሆን አግባብ ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር ይሰራል፣
- የአካባቢ ጥበቃ ከግምት ውስጥ ያስገቡ ሆነው ተመጣጣኝ ዋጋና ብቃት ያላቸውን የኢነርጂ ምንጮችና ቴክኖለጂዎችን ልማት፣ ስርጭት፣ አጠቃቀምና ቁጠባ ያጣራል፣ እንደሁኔታው በግል ባለሀብቶች፣ በመንግስትና በሌለች ዘርፎች በኩል ለህብረተሰቡ ያስተዋውቃል፣
- ኢነርጂን የሚመለከቱ መረጃዎችን ይሰበስባል፣ ያጠናቅራል፣ ይተነትናል፣ እንደ አስፈላጊነቱ ለተጠቃሚዎች ያሰራጫል፡፡